December 9, 2018

የቤተጊዮርጊስ ግድግዳ ቁስሎች/ጠባሳዎች/

ቤተሥላሴ Naod

በቤተጊዮርጊስ ህንጻ ግድግዳ ላይ የሚታዩት አብዛኛዎቹ ትኩስ ቁስሎች፤ ከእድሜ ብዛት የሚመጡ መፈራረሶች አይደሉም! ይልቁንም በሥርዓተ ቁፋሮ (ሥቁ) ጊዜ የደረሱ ጉዳቶች እና ጠባሳዎች እንጂ። ወደዚህ ድምዳሜ ያደረሱኝን ማስረጃዎች እና የፎቶግራፍ ማስረጃዎች በዚህ ጦማር አቀርባለሁ።እኒህን ጠባሳዎች ለመጠገን ሙከራዎችም እንደተደረጉ አይቻለሁ። ይህንንም እንድጽፍ ያስደረገኝ አንዱ ነገርም ቅርሶች ታሪክ የሚናገሩት በውበታቸው ብቻ ሳይሆን በጉዳታቸው ጭምር እንደሆነ ለማሳየት፤ ወደፊትም የቅርሶች ጥገና ሲታሰብ መጀመርያ ተጎዳ የተባለው ቅርስ ጉዳቱን ብቻ ሳይሆን በጉዳቱ ሳቢያ የሚናገረውን ታሪክ ማጥናት ወይም መረጃ መሰብሰብ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ለማሳሰብም ነው።

 በዚህ ጦማር የምዳሣቸው ሦስት ዓይነት ጠባሳዎች ናቸው። እነርሱም፦
1ኛ/ ደረጃ ሥር ያሉ ጠባሳዎች
2ኛ/ መስኮት ሥር ያሉ ጠባሳዎች
3ኛ/ ሦስተኛ ደርብ ላይ ያሉ ልዩ ጠባሳዎች


በህንጻው ውኃልክ እና ደረጃዎች ስር ያሉ ግድግዳዎች ላይ ትልልቅ ጠባሳዎች አሉ። ለመጀመርያ ጊዜ የሚያያቸው ሰው ህንጻው ጥንታዊ ከመሆኑ የተነሳ የሚታይ የእርጅና ምልክት መስሎ ሊታየው ይችላል። በጣም ለቅርስ ክብካቤ የሚቆረቆርም "አረ እየፈረሰ ነው!" ብሎ ሊጨነቅ ይችላል። እኒህ ጠባሳዎች ግን የመፍረስም ሆነ የእርጅና ምልክቶች አይደሉም፤ ሆን ተብለው በሰው የተቆረቆሩ፤ የተቦረቦሩ እንጂ። ይህንንም የሚጠቁሙት ምልክቶች
1ኛ/ የተቦረቦሩት ቅርጾች ተመሳሳይነት
2ኛ/ አንዳንዶቹ ላይ ተጨማሪ ጌጥ ሁሉ የተበጀላቸው መሆኑ
3ኛ/ ያን ቅርጽ ለመፍጠር የሚያስገድድ ልዩ የጎርፍም ሆኖ የአለት ባህርይ ለውጥ አደጋ አለመኖሩ ነው።
ከዚህም በመነሳት የምሰጠው መላምት
እኒህ ጠባሶች የተፈጠሩት በህንጻው ቁፋሮ ጊዜ ለርብራብነት በተጋደሙ ግንዲላ እንጨቶች ምክንያት በደረሰባቸው ፍትጊያ ወይም ግንዶቹ ጸንተው እንዲቆሙ ለማድረግ የተቆፈሩ መደገፊያ ቀዳዳዎች ናቸው።  
እኒህ የግንድ ርብራቦች አንዱ ጫፋቸው ከህንጻው ጋር ሲሆን፤ ሌላው ጫፋቸው ደግሞ ከግቢው ግድግዳ ጋር ካሉት ዋሻዎች ጋር ይገጥማል። በየግድግዳው ላይ ያሉ ዋሻዎቹ የተፈጠሩት ለዋሻነት አይደለም የሚል ነጥብም ባለፉት ጦማሮች ላይ ያነሳሁትም ለዚሁ ነው።
  
በዘጠኙ ድፍን መስኮቶችም ሥርም እንዲሁ ልዩ ትኩረትን የሚስቡ ጠባሳዎች ይገኛሉ። የእኒህ ጠባሳዎችም ልዩ በሕርይ
1ኛ/ በእያንዳንዱ መስኮት ሥር ሁለት ሁለት ጠባሳ ብቻ ነው ያለው
2ኛ/ እያንዳንዱ ጠባሳ በአራት መዓዘን ጉጦች ሥር እና ትክክል ነው የሚገኘው
3ኛ/ ጠባሳዎቹ ሆን ተብለው የተቆፈሩ እና የክብነት ቅርጽ ያላቸው ናቸው።
ከዚህም የተነሳ እኒህም ጠባሳዎች የተፈጠሩት ከላይ በስዕል ባመለከትኩት መሰረት በሥርዓተ ቁፋሮ ጊዜ በተረበረቡ ግንዶች ምክንያት ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ።     

እኒህን ጠባሶች ለመጠገን ሙከራ እንደተደረገ በግልጽ የሚታይ ነገር ነው። ወደፊትም ቅርስ ተንከባካቢዎች "እንጠግን" ባሉ ጊዜ ሁሉ የሆነ ሲሚንቶ እየለጠፉ ሊደፍኗቸው እንደሚሞክሩ ጥርጥር የለውም (እኔ ባይመቸኝም)። ከሁሉ አስቀድሞ ግን ከላይ በጠቀምኩት እና በሌሎችም ጥናቶች እኒህ ጠባሳዎች የሚናገሩትን ታሪክ በትክክል መረዳት ወይም መዝግቦ ማስቀመጥ አንዱ እና ዋነኛው የቅርስ ጥበቃ ስልት ይመስለኛል። 
በደረጃዎቹ ሥር ከሚገኙ ጠባሳዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ተጨማሪ ቁፋሮ ተካሂዶባቸው ለሌላ ጥቅም እንዲውሉ እንደተደረገም ይታያል። እኒህን ቅርጾች የተቦረቦሩት በላሊበላ ዘመን ይሁን ከዚያ ዘመን በኋላ፤ እንዲሁም የተቦረቦሩበት ዓላማ ለመቃብርነት ይሁን ወይ ለሌላ አገልግሎት ተጨማሪ ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ ሆኖ ነው ያገኘሁት።  

ካየኋቸው የቤተጊዮርጊስ የጉዳት ምልክቶች ሁሉ እውነተኛ ጥፋት የሚመስለኝ አንድ ነገር ከታች በፎቶ ያሳየሁት የተጎመደ አራት መዓዘን ነው። ይህን የመስኮት ጌጥ የጎመደው በእርግጠኝነት ምን እንደሆነ ለማረጋገጥ ባልችልም፤ ከላይ ከጉድጓዱ ጫፍ ላይ ተገምሶ የወደገ አለት የፈጠረው ጉዳት እንደሆነ ሰምቻለሁ። 

በመጨረሻ በህንጻው ሦስተኛ ደርብ ላይ ያስተዋልኩት አንድ ለየት ያለ ጠባሳ አለ። ጠባሳው የህንጻውን ጠርዝ የቸረቸፈ ስለሆነ አስቤ አስቤ ላገኝነት የቻልኩት ማብራርያ "የመወጣጫ ርብራብ የተንተራሰበት እና ጠርዝ ሥስ ስለሆነ በቀላሉ የቸረቸፈው ሊሆን ይችላል የሚል ነው። ከታች ያለው ፎትግራፍ የሚያሳየው ይህን የጠርዝ ጠባሳ ሲሆን በ3ዲ የነደፍኩትም ጉዳቱ የተከሰተበትን ምክኛት ለማሳየት የሰጠሁትን መላምት ነው።  

"‹እግዚአብሔርም፤ ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ›› ዘፍ1፡-3